BBC Amharic – የቴክኖሎጂ ነገር- ሀበሻ ኢን ቴክ

ቴክኖሎጂን የተመለከቱ ውይይቶች ብዙ አይደሉም። ባሉትም የሚሳተፉት ጥቂቶች ናቸው።

ካናዳ በሚገኝ ባንክ ውስጥ በክላውድ ኢንተግሬሽን ክፍል ከፍተኛ ኃላፊ የሆነው ተፈሪ በቀለ ካሳ፤ ሀበሻ ኢን ቴክ የተባለ የክለብሀውስ ገጽ የከፈተውም የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እንዲገናኙ ነው።

ባለሙያዎቹ የገጠሟቸውን ፈተናዎች እና ስኬታቸውን ያካፍላሉ። ከአድማጮች መካከል ባለሙያዎቹ በተማሪነት (ሜንተርሺፕ) የሚወስዷቸውም አሉ። 

ተፈሪ ክለብሀውስ ላይ የሚደረጉትን ውይይቶች ቀድቶ ወደ ፖድካስት ይወስዳቸዋል።

“ማይ ቴክ ጆርኒ ወይም የእኔ የቴክኖሎጂ ጉዞ በሚል ሰዎች እየተጋበዙ ያወራሉ። በቴክኖሎጂው ስኬታማ ሰዎች ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት ነው።”

በሳይበር ሰኪውሪቲ፣ በክላውድ ኮምፒውቲንግ እና በሌሎችም የቴክኖሎጂ ዘርፍች ውይይት ይደረጋል።

እስካሁን ከጋበዛቸው ባለሙያዎች መካከል የሊንክድኢን ዳይሬክተር ኦፍ ኢንጂነሪንግ በፍ አየነው፣ ሊሊ አምደማርያም፣ የቴክቶክ አዘጋጅ ሰለሞን ካሳ፣ አዲስ ዓለማየሁ፣ ማርቆስ ለማ፣ የቅኔ ጌምስ ፈጣሪ ዳዊት አብርሀም ይጠቀሳሉ።

የቴክኖሎጂ ሙያተኞች ስለ ሥራቸው በፌስቡክ ወይም በሌላ ማኅበራዊ ሚዲያ ከመጻፍ ስለሚቆጠቡ እንደ ክለብሀውስ ያሉ ገጾች ተመራጭ እየሆኑ እንደመጡ ይገልጻል።

ክለብሀውስ በሙያው ውስጥ ካሉ እና ቴክኖሎጂ ከሚወዱ ሰዎች ጋር መነጋገር የሚችሉበት ነው።

ክለብሀውስ ተወዳጅ መሆኑ ሌሎች መተግበሪያዎች ላይ ያሉ የድምጽ ውይይት መድረኮችን እንዳስተዋወቀ ተፈሪ ይናገራል። የስፖቲፋዩ ግሪንሩም እና የትዊተሩ ስፔስ ይገኙበታል።

ከፌስቡክ እና ከዩቲዩብ በተለየ ክለብሀውስ አሳታፊ ነው። ሐሳብ ከአንድ ወገን ብቻ የሚመነጭበት ሳይሆን የንግግር መድረክነቱ ያመዝናል።

“እውቀት ተኮር በሆኑ ጉዳዮች ከላይክ እና ከኮሜንት ባለፈ እርስ በእርስ ለማውራት ስለሚመች ተመራጭ እየሆነ መጥቷል” ሲል ያስረዳል።

በሀበሻ ኢን ቴክ በየሳምንቱ ከ50 እስከ 100 ሰዎች ይሳተፋሉ።

“እኔ የማረጋግጠው እኔ መኖሬን፣ ሚስቴ መኖሯን እና እንግዶቼ መኖራቸውን ነው። ሌላው ሰው በራሱ ፕሮግራም ወይም ፍላጎት ነው የሚመጣው።”

ቀጣይነት ያለው እና ባስፈለገ ጊዜ የሚገኝ የቴክኖሎጂ መድረክ መፍጠሩን የሚገልጸው ተፈሪ፤ ሀበሻ ኢን ቴክ በቀዳሚነት የጠቀመኝ እኔን ነው ይላል።

“እንግዶቼ ስለ ብርታታቸው ሲያወሩ፣ የወደቁበትን ሲያወሩም ብዙ ተምሬያለሁ። ከእንግዶቼ ጥሩ ምላሽ አግኝቻለሁ። አበረታተውኛል። አድማጮችም እንደሚያነሳሳቸው ይነግሩኛል።”

የክለብሀውስ መስራቾች ገጹን የሚያስተዋውቁት ‘በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ አስደናቂ ነገሮች እያወሩ ነው። እየሮጡ ወይም እየተራመዱም ቢሆን ያዳምጡ። እርስዎም ሐሳብዎን ያካፍሉ’ በማለት ነው።

ንግድ እንዴት ያድጋል? ናይጄርያ እና ፖሊሶቿ፣ ሂፕ ሀፕ ሙዚቃ የሚሉና በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ገጾች በየቀኑ ያገኛሉ።

ተፈሪ በበኩሉ ክለብሀውስን የሚገልጸው “እዚህ ቦታ ድምጽ አለኝ የሚል ስሜት ይፈጥራል” ብሎ ነው።

Source: BBC

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *